ወደ ገላትያ ሰዎች
፩
፩-፫ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ፬ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ። ፭ ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ፮ በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ ፯ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ፰ ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። ፱ አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። ፲ ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ፲፩ ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ፲፪ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። ፲፫ በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ ፲፬ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር። ፲፭-፲፯ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። ፲፰ ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ፲፱ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። ፳ ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም። ፳፩ ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። ፳፪ በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ ፳፫ ነገር ግን። ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ፳፬ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።